መጀመሪያው አለም አቀፍ ኢትዮ-የሆርቲካልቸር ኮንፈረንስ ሊካሄድ ነው

መጀመሪያው አለም አቀፍ ኢትዮ-የሆርቲካልቸር ኮንፈረንስ ሊካሄድ ነው

 

 

ኦቢኤን የካቲት 17፣2012-የመጀመሪያው አለም አቀፍ ኢትዮ- የሆርቲካልቸር ኮንፈረንስ በአዲስ አበባ በስካይላይት ሆቴል የካቲት 20 እና 21/2012 ዓ.ም እንደሚካሄድ የግብርና ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

ኮንፈረንሱ በኢትዮጵያ ግብርና ሚኒስቴር እና በሆርቲካልቸር አምራች ላኪዎች ማህበር ጋር በመተባበር የተዘጋጀ መሆኑን የግብርና ሚኒስቴር ሚኒስትር ድኤታ ወ/ሮ አይናለም ንጉሴ ተናግረዋል፡፡

በመርሃ-ግብሩ የመንግስት ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች፣ ከተለያዩ አገራት የሚመጡ እንግዶች፣ በዘርፉ የተሰማሩ አምራችና ላኪዎች፣ የፋይናንስ ተቋማት፣ ኢንቨስተሮች እና ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ተመራማሪዎች እንደሚገኙ ወ/ሮ አይናለም ንጉሴ ገልፀዋል፡፡

ሚኒስትር ድኤታዋ ሆርቲካልቸር ለአገር ኢኮኖሚና ለስራ ዕድል ፈጠራ ከፍተኛ አስተዋፅዖ በማድረግ ላይ ያለ ዘርፍ መሆኑን ጠቅሰው ዘርፉን የበለጠ ውጤታማ ለማድረግ ኢትዮጵያ ለሆርቲካልቸር የተመቸ አግሮ ኢኮሎጅ ያላት መሆኑን የማስተዋወቅ ስራ ይሰራል ብለዋል፡፡

በዘርፉ የተሰማሩ አካላት ያስገኙት ውጤትና ያጋጠማቸውን ችግሮች በተመለከተ ውይይት እንደሚደረግም ተገልጿል፡፡ ከውይይቱ በመነሳት በመንግስት ተቋማትና በዘርፉ ተዋናኞች መስተካከል ያለባቸው ጉዳዮች ተለይተው የመፍትሄ አቅጣጫ እንደሚቀመጥም በጋዜጣዊ መግለጫው ተነስቷል፡፡

የሆርቲካልቸር ልማት ለአገራችን ኢኮኖሚና የስራ ዕድል በመፍጠር ረገድ ከፍተኛ አስተዋፅዖ እያደረገ ያለ ዘርፍ ነው ብለዋል ሚኒስትር ድኤታዋ፡፡ የሆርቲካልቸር ዘርፍ ከቡና ቀጥሎ ከፍተኛውን የውጭ ምንዛሬ የሚያስገኝ በመሆኑ በአገራችን ኢኮኖሚ ላይ ከፍተኛ አስተዋፅዖ እንዳለውም ወ/ሮ አይናለም ንጉሴ ተናግረዋል፡፡

ኮንፈረንሱ በዘርፉ ላይ የተሰማሩ እና አስተዋፅዖ ሊያደርጉ የሚችሉ በአገር ውስጥ እና በውጭ ያሉ አካላትን በማግኘት በችግሮቹ ላይ ለመነጋገር የሚያስችል መድረክ መሆኑም ተነግሯል፡፡

የግብርና ሚኒስቴር ከሚሰራቸው ስራዎች አንዱ እና ዋናው የዘርፉን ምርትና ምርታማነት ለማሳደግ የሚያስችሉ የግብርና ግብዓቶችን ማቅረብ መሆኑን ወ/ሮ አይናለም ንጉሴ ገልፀው ከዚህ ውስጥም ትልቁን ድርሻ የሚወስደው የማዳበሪያ አቅርቦት መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የ2012/13 ለምርት ዘመን ለአማራ፣ ኦሮሚያ፣ ደቡብ እና ቤ/ጉሙዝ እንዲሁም ለንግድ እርሻዎችና ለግል እርሻዎች አገልግሎት ሊሰጥ የሚችል 14.5 ሚሊየን የአፈር ማዳበሪያ ኩ/ል እንደሚያስፈልግ ተገልጿል፡፡

የአፈር ማዳበሪያዎቹ ከግብርና ስራዎች ኮርፖሬሽን ጋር በመሆን የግዢ ሂደቱ እንደተጠናቀቀ ሚኒስትር ድኤታዋ ተናግረው ማዳበሪያዎቹ በ26 መርከቦች ተጓጉዘው ወደ ሃገር ውስጥ እንደሚገባ መናገራቸውን ከሚኒስቴሩ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡(ኢ.ፕ.ድ)

Facebook Comments